መጤ ወራሪ ዝርያን የማስወገድ ስራ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው እየተሰራ ነው ተባለ

ግሎባል ኤቢኤስ ከጀነቲክ ሀብት አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የምክክርና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ በኢትዮጵያ 35 መጤ ወራሪ ዝርያዎች እንዳሉ ተነግሯል፡፡

ወራሪ መጤ ዝርያዎች ሀገር በቀል ዝርያዎችን በመውረር እንዲጠፉ በማድረግ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ እነዚህ ዝርያዎች በተለያዩ መንገዶች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ሲሆን የስርጭትና የጉዳት መጠናቸው እንደየስርዓተ-ምህዳር ይለያያል፡፡

በመድረኩ ላይ ስለ መጤ ወራሪ ዝርያዎች በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ገለፃ ያቀረቡት የእፅዋት ተመራማሪ የሆኑት  አቶ አማረ ሰይፉ ሲያብራሩ ወራሪ ዝርያዎችን ከተከሰቱ በኋላ ከማስወገድ ይልቅ ቀድሞ መከላከል ተመራጭ ስራ ነው ብለዋል፡፡ ወራሪ መጤ ዝርያዎች በከፍተኛ ፍጥነት የሚራቡ፣ የተለያዩ የአየር ንብረቶችን በቀላሉ መላመድ የሚችሉ፣ ዘራቸው ለረጅም ጊዜ ሳይሞት ለዓመታት መቆየት የሚችል መሆናቸውና ሌሎች ባህርያቶቻቸው የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከተለያዩ የብዝሀ ሕይወት ማዕከላት፣ ከጉምሩክና አየር መንገድ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች እንዲሁም ከተለያዩ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የተገኙ ተሳታፊዎች ስለ መጤ ወራሪ ዝርያዎች ያላቸውን አስተያየት አቅርበዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ ሀገራችን ውስጥ ያለው ግንዛቤ፣ ስለ ስርጭት መጠናቸው፣ ምን ህያል ጉዳት እንደሚያደርሱ ያለው ግንዛቤ በጣም አናሳ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በየጊዜው ወራሪ መጤ ዝርያዎችን ከመከላከል ወይም ከተከሰቱ በኋላ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከማድረግ ይልቅ ጨርሶ ለማጥፋት የሚደረጉ ስራዎችና አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ ተብሎ የተጠየቀ ሲሆን ዝርያዎቹ በተለይ እንቦጭ አረምን ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ የሚቻል ቢሆንም ሌሎች ብዝሀ ሕይወቶችን የሚያጠፉበት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ማስወገዱ ይመረጣል የሚል ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡

መጤ ወራሪ ዝርያዎች ባህሪያቸው በጣም ተለዋዋጭ በመሆኑ ባህሪያቸውን ይበልጥ ለመረዳትና የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ከምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከክልሎች፣ ከግብርና ተቋማት እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እብሮ በመስራት ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ይበልጥ መሰራት አለበት ተብሏል፡፡

 

አቶ አሸናፊ አየነው

አቶ አማረ ሰይፉ

አቶ ተስፋዬ በቀለ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *