የሸኮ ዳልጋ ከብት ንዑስ ዝርያ ጥበቃና ማሻሻል መማክርት መተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ ሰነድን ለማዳበር የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ

      Comments Off on የሸኮ ዳልጋ ከብት ንዑስ ዝርያ ጥበቃና ማሻሻል መማክርት መተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ ሰነድን ለማዳበር የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የመሰብሰቢያ አዳራሽ መጋቢት 20 ቀን 2011ዓ.ም የተደረገውን የውይይት መድረክ ያስተባበሩት በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የእንስሳት ብዝሀ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብረሀም አሰፋ እንዳሉት የሸኮ ዳልጋ ከብት ንዑስ ዝርያ ጥበቃና ማሻሻል መማክርት ማቋቋም ያስፈለገበት ዋነኛ ዓላማ የሸኮ ዳልጋ ከብት ንዑስ ዝርያ ጥበቃ፣ዘለቂታዊ አጠቃቀምና የምርምር ሥራዎችን በመደገፍ ዙሪያ የሚሰሩ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ለማሰባሰብና በንኡስ ዝርያው ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን በቅንጅት ማከናወን እንዲቻል ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አብረሀም ገለጻ የሸኮ ዳልጋ ከብት ዝርያ ቁጥር በመናመን ላይ የነበረ ዝርያ የነበር ቢሆንም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በተሰራው ውጤታማ ሥራ ቁጥሩ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው ወደ ትክክለኛ ወይም ወደሚፈለገው ቁጥር እንዲደርስ ለማድረግ የዚህ መማክርት መቋቋም እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
አቶ አብረሀም አክለውም የመማክርቱ መቋቋም የአርቢዎች ማህበርን ለመመስረት ጥርጊያ መንገድ የሚከፍት መሆኑንና በቀጣይም በዝርያ እርባታና በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላትን አሰባስቦ ወደ አርቢዎች ማህበር ለመቀየርና ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የመተዳደሪያ ደንቡ ዝግጅት ሲጠናቀቅም በአስተባባሪነት ከሚመራው ከደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና አየር ለውጥ ቁጥጥር ባለሥልጣን ፣ ከኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ ከደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ቢሮ ፣ከደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የግብርና ምርምር ተቋም ፣በየወረዳው ከሚገኙ የብዘሀ ሕይወት የሥራ ሂደት ባለሙያዎች፣ በየወረዳው ከሚገኙ የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ባለሙያዎች እና ከፌዴራል የአካባቢ ደንና አየር ለውጥ ኮሚሽን የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀርቦ የሚጸድቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመማክርቱ መተዳደሪያ ረቂቅ ሰነድ በደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና አየር ለውጥ ቁጥጥር ባለሥልጣን የእንስሳት ባለሙያ በወ/ሮ ጽጌረዳ በቀለ እና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ዘርፍ ተመራማሪና መምህር በአቶ አሰፋ ታደሰ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡