በቀጥታ በድረ-ገጽ የአርክቦት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ

ግሎባል ኤቢኤስ ከጀኔቲክ ሀብት አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ያለኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ፈቃድ ማንኛውንም ጀኔቲክ ሀብት በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ማስወጣት የተከለከለ እንደሆነ ነው የተገለፀው፡፡

ሀብትን ለመጠበቅ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው መስርያ ቤቶች  የኢንስቲትዩቱ ፈቃድ ባያስፈልጋቸውም ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ወይም ከሀገር ማስወጣት እንደማይችሉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የጀነቲክ ሀብት አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አየነው እንዳስረዱት ጀነቲክ ሀብትን ለማርከብ በቅድሚያ የኢንስቲትዩቱ አስቀድሞ፣ተገንዝቦ የሚሰጥ እሺታ ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አንድ ምርምር በላብራቶሪ እጥረትም ሆነ በሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ምክንያት ምርምሩ ከሀገር ውጪ መከናወን ካለበት ብቻ የጀኔቲክ ሀብት በህጋዊ መንገድ ከሀገር ሊወጣ ይችላል፡፡ በዚህም መሠረት ጀኔቲክ ሀብቱ እንዲወጣ በፈቃጁ እና ምርምሩን በሚያከናውነው አካል የአርክቦቱ ህጉ አንዳይጣስ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ፡፡

ከመጋቢት 13-14/2011ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተካሄደው የምክክርና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ጀነቲክ ሀብት የማህበረሰብ እውቀት አርክቦትና የማህበረሰብ መብቶች አዋጅ ቁጥር 482/1998 ላይ የተዘረዘሩት አርክቦትን የመቆጣጠር መብቶች፣ ጀነቲክ ሀብትን የመጠቀም መብት፣ ጥቅም የመጋራት መብት፣አርክቦት ስለሚፈፀምበት ሁኔታ፣ ስለ ቅድመ ሁኔታዎች፣ የአርክቦት ፈቃድ ስለመስጠት፣ የተለየ የአርክቦት ፈቃድ፣ ስለ የኳረንቲን ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች እና ሌሎች ሀሳቦችን የሚያነሱ አንቀጾች ተብራርተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የአርክቦት ህግ የናጎያ ፕሮቶኮልም ስለሚያነሳቸው ህጎች ገለፃ ተሰጥቶበታል፡፡

በጉምሩክ ስር የሚገኙ አንዳንድ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ሰራተኞች እንዲሁም የአየር መንገድ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ሰራተኞች በኩል ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን በመድረኩ የተሳተፉ አካላት ገልፀዋል፡፡ ከሀገር የሚወጡ መንገደኞች ጀነቲክ ሀብትን የሚይዙበት ሁኔታ ረቂቅ መሆኑና ጀነቲክ ሀብት የሚለው አጠራር በራሱ ለሰራተኞቹ ግልፅ እንዳልሆነ ጠይቀው ግንዛቤውን ለማስፋት የይበልጥ እንደሚሰራ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜያት ጀነቲክ ሀብትን ህጋዊ በሆነ መንገድ የአርክቦት ጥያቄዎችን ለማስተናገድና ጥቅም ላይ ለማዋል  በኮምፕዩተር የታገዘ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡

አቶ ጌትነት አባተ

የመድረኩ ተሳታፊዎች

የመድረኩ አወያዮች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *