የኢትዮጵያ ብዝሀሕይወት ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች የ2011 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያዩ

በኢንስቲዩቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሚያዝያ 8 ቀን 2011ዓ.ም ለግማሽ ቀን በተደረገው ውይይት ላይ ሪፖርቱን ያቀረቡት የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ አልማዝ ተስፋዬ ናቸው፡፡ ወ/ሮ አልማዝ ባለፉት 9 ወራት የ5ቱ ዒላማ ፈጻሚ እና ድጋፍ ሰጪ ዳይሬክቶሬቶችን እቅድ ክንውን ያቀረቡ ሲሆን በእቅዳቸው መሠረት የአበይትና የለውጥና መልካም አስተዳደር የሥራ አፈጻጸማቸው በተሻለ ሁኔታ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከኤፍ.ሚ.ስ ጋር ተያይዞ ለምርምር የሚውሉ እቃዎች የግዢ መዘግየት ባለፉት 9 ወራት ያጋጠመን ችግር ነው ያሉት ወ/ሮ አልማዝ ይህንንና ሌሎች በፋይናንስ ክፍል የሚታይ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የፋይናንስ ሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር ማከናወን መቻሉን እንደ መፍትሄ አንስተዋል፡፡
ወ/ሮ አልማዝ በኢንስቲትዩቱ ግቢ ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የእንስሳት እና የደቂቅ አካላት ዘመናዊ የምርምር ላብራቶሪ የግንባታ ሂደት የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ በ2011 በጀት ዓመት 12.5 ከመቶ ለመፈጸም ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 11.08 በመቶ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡት የለውጥና መልካም አስተዳደር የቅሬታና አቤቱታ ባለሙያ አቶ መሀመድ ኢብራሂም በበኩላቸው የ1ለ5 ውይይት መደረጉን፣እቅድን የማስተዋወቅና ወደ ሁሉም ፈጻሚዎች የማውረድ ሥራ መከናወኑን፣ የሳምንታዊና የሩብ ዓመት ዕቀድ ክንውን ግምገማ በየስራ ክፍሉ መካሂዱን እና ሠራተኞችን በየሥራ ዘርፋቸው ማደራጀት መቻሉን ፣ ለተነሱ 4 ቅሬታዎች ምላሽ መሰጠቱን እና ለውስጥና ለውጭ ተገልጋዮች ፈጣን ምላሽ መስጠት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በኢትዮጵያ ብዝሀሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማሪዮና በሚመለከታቸው የስራ ክፍል ሀላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *