የጨው ማምረት ሥራ በአፍዴራ ሐይቅና አካባቢው ሥርዓተ-ምህዳር ላይ ያለው ተጽዕኖ

የሐይቅ ሥርዓተ-ምህዳር እጽዋቶች፣ እንስሳቶች እና ደቂቅ አካላት በአንድ ላይ የሚኖሩበት ቦታ በመሆኑ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የውሃ ውስጥ እንስሳት፣ የዱር እንስሳትና የሰው ልጆች የዚህ ሥርዓተ-ምህዳር ዋነኛ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ሐይቆች ዘርፈ ብዙ የሆኑ ጥቅሞችን እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ለመጠጥ ውሃ፣ መሬትን በመስኖ ለማልማት፣ አሳ ለማርባት፣ ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ግብአትነት፣ ለመዝናናት፣ ለባህላዊ እሴትና ለተለያዩ የሳይንስ ምርምሮች ይውላሉ፡፡ በመሆኑም በሐይቆች ሥርዓተ-ምህዳር ላይ የሚደርስ ምንም አይነት ለውጥ ለምሳሌ የመጠን፣ ኬሚካላዊና ባዮሎጂካዊ ለውጦች ከፍተኛ የሆነ የአካባቢና ማህበራዊ ቀውሶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡

ከፍተኛ የጨው መጠን ካላቸው ሐይቆችና ባሕሮች ላይ ውሃን በመጥለፍ ወይም በሞተር ኃይል በመሳብና ማትነኛ ቦታ በማዘጋጀት (Solar Pond) በማጠራቀም በንፋስና በፀሐይ ኃይል ውሃው እንዲተን አድርጎ ከስር የሚቀረውን ጨው በሰው ጉልበት መሰብሰብና ጥቅም ላይ ማዋል ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን እና እጅግ በጣም አነስተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ባላቸው ቦታዎች ላይ የሚተገበር የጨው ማምረት ዘዴ ነው፡፡ የዓለማችን 1/3ኛው የጨው ምርት በዚህ ዘዴ እንደሚመረት ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የአፍዴራ ሐይቅ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የሚገኝ ሐይቅ ሲሆን አካባቢው ከባህር ጠለል በታች 126 ሜትር (-126 ሜትር) ዝቅ ብሎ በደናክል ዲፕሬሽን (Danakil Depression) ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ሐይቅ ከፍተኛ (130.25g/lit) የሆነ ጨዋማነት ባህሪ ስላለው ከላይ በተጠቀሰው ዘዴ አማካኝነት የጨው ምርት እየሰጠ ይገኛል፡፡

የአፍዴራ ሐይቅ በዙሪያው የሚገኝ ምንም አይነት ገባር ወንዝ የሌለው ቢሆንም፣ በዙሪያው (ከ20-50 ሜትር) ዙሪያ የሚገኙት የፍል ውሃ ምንጮችና የከርሰ ምድር ውሀ መጠኑን ጠብቆ እንዲኖር ይረዱታል፡፡ እነዚህ የፍል ውሀ ምንጮች ሐይቁን ከመመገብ በተጨማሪም በውስጣቸው Danakilia franchettii እና Aphanius stiassnyae የሚባሉ በአፍዴራ ሐይቅ ሥርዓተ-ምህዳር ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የአሳ ዝርያዎችን ይዘዋል፡፡

እነዚህ ብርቅዬ የአሳ ዝርያዎች በአካባቢው ካለው ሰው ሰራሽ ተፅዕኖ የተነሳ “በአደጋ ላይ ያሉ” የአሳ ዝርያዎች ተብለው በዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ህብረት (IUCN) ተመዝግበዋል፡፡ በተለይ በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው በአፍዴራ ሐይቅ ዙሪያ ለሚካሄደው የጨው ማምረት ሥራ የሚያገለግሉ የውሀ ማትነኛ ቦታዎችን/ጉድጓድ (Solar Ponds) ለማዘጋጀት ሲባል በርካታ የፍል ውኃ ምንጮች እየጠፉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ በውስጣቸው የሚገኙትን ብርቅዬ የዓሳ ዝርያዎች ጭምርም በማጥፋት ላይ ይገኛል፡፡ ሐይቁንና አካባቢውን ከጥፋት ለመታደግ የጨው ማምረቱ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ቦታ የተወሰነ ቢሆን እና ይህንንም ለማስፈጸም የሚረዳ መመሪያ ሊዘጋጅለት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተወሰኑ የሐይቁ ዳርቻዎች በሰሜን-ምዕራብና ምስራቅ አካባቢዎች ጥብቅ ሆነው ከማንኛውም የሰው እንቅስቃሴ የጸዳ ቢሆን አካባቢውን ከጥፋት ለመታደግ ያስችላል፡፡ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከአካባቢው ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፡፡ በጥናቱ መሰረትም ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት የዘቦታ ማንበር ሥራው ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር በቀጣይ ሁሉም በአካባቢው የሚገኙ ማህበረሰቦችና ባለድርሻ አካላት ያልተቆጠበ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *