የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከማህበረሰብ ዘር ባንክ አባል አርሶ አደሮች ጋር ተወያየ

ማህበራዊ ነባር ዘር ባንክ

ማህበራዊ የዘር ባንክ አባላት

ማህበራዊ የዘር ባንክ አባላት

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በደብረብርሀን ከተማ አንኮበር እና ሲያደብር ወረዳዎች በመገኘት ከነባር ዘር ተንከባካቢ አርሶ አደሮች ጋር በማህበረሰብ ዘር ባንክ አያያዝ እና የባለድርሻ አካላት ሚና ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የአዝርዕት እና ሆርቲካልቸር ዳይሬክቶሬት የማህበረሰብ ዘር ባንክ አሰተባባሪ አቶ ውብሸት ወንድሙ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ነባር ዘር ማለት ጥንት አያቶቻችን ሲጠቀሙበት የነበረ ዘር ሲሆን ነገር ግን በአሁን ጊዜ የነባር ዘር ተጠቃሚነታችን እየጠፋ በሚያስብል ሁኔታ ላይ ደርሷል፡፡ ይህም የሆነበት ከምርጥ ዘር መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለነባር ዘር የሚሰጠዉ ትኩረት እየቀነሰ መምጣቱ እንደትልቅ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡

ማህበራዊ ዘር ባንክ አርሶ አደሩ ዘሩን ሰብስቦ ጎተራዉ ላይ የሚያጋጥመውን የምርት ብክነት ለመከላከል በማህበራዊ ዘር ባንክ ውስጥ ለማከማቸት ያስችላል፡፡ ወጣቶች እና ሴት አርሶ አደሮች ከማህበረሰብ ዘር ባንክ ነባር ዘርን በመውሰድ አምርተው የተጠቀሙበትን ዘር ወደ ማህበራዊ ዘር ባንክ በመመለስ የነባር ዘር ዋስትና እንዳይጠፋ እንዲሁም አርሶ አደሩና የአካባቢዉ ማህበረሰብ የምርት ተጠቃሚ እንዲሆን ማህበራዊ ዘር ባንክ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

ከምርጥ ዘር ጎን ለጎን ነባር ዘርም እንዳይጠፋ ሁለቱንም በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል አቶ ውብሸት ተናግረዋል፡፡

አቶ ውብሸት አክለውም በእርሻ ስራ ወቅት ለምርጥ ዘር የሚያስፈልገውን ዓይነት የማሳ ዝግጅት ነባር ዘርም ያስፈልገዋል፡፡ ዘሩም በሚዘራበት ወቅት ወቅቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበትና ስንዴንም ሆነ ጤፍ በብተና ከሚዘራ ይልቅ በመስመር መዝራት በምርት አሰጣጥ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ብለዋል፡፡ ለምርጥ ዘር የሚደረገው ጥንቃቄ ለነባር ዘርም እንደሚገባና ሰብሉ ከደረሰ በኋላም በአጨዳና ውቂያ ወቅት እንዲሁም ወደጎተራ ሲገባ የሚኖረውን ብክነት መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የወረዳዎቹ አስተዳደር የግብርና ልማት፣ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ፣መሬት አስተዳደር፣ አካባቢ ጥበቃ፣ የማህበራት ማደራጃ፣ ንግድ ቢሮ፣ ሴቶችና ህፃናት እንዲሁም ዩኒቨርሰቲዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የማበህረሰብ ዘር ባንክ ባለድርሻ አካላት በመሆናቸው ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *