የመስቀል ወፍ

      No Comments on የመስቀል ወፍ

የመስቀል ወፍ

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የአዲስ አመት መቀበያ የመጀመሪያው ወር መስከረም ከሌሎች ወራት በተለየ መልኩ በተፈጥሮ ውበት ያሸበረቀ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የመስከረም ወር የክረምቱ መገባደጃ በመሆኑ በዕፅዋት አበባዎች በተልይም የአደይ አበባ የሚያብብበት በመሆኑ ለአይን ማራኪ ወቅት ነው። ከአደይ አበባ ውበት በተጨማሪም የመስከረም ወርን ለየት ከሚያደርጉት ነግሮች አንዱ ከወትሮው ለየት ያሉ ለአይን የሚማርኩ የአፅዋፋት ዝርያዎች (የመስቀል ወፍ) የሚታዩበት መሆኑ ነው።

አንዳአንድ ተባዕታይ የወፍ ዝርያዎች የላባቸውን ቀለም በመቀየር ወይም የጅራታቸውን ላባ በማሳደግ ከወትሮው ለየት ብለው በዓመት አንዴ በመስከረም ወር ይታያሉ። እነኚህ የወፍ ዝርያዎች በተለምዶ የመስቀል ወፍ ተብለው ይጠራሉ።

የመስቀል ወፍ መስከረምን ጠብቀው ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሳይሆኑ ዓመቱን ሙሉ በሚገኙበት ቦታ የሚኖሩ ናቸው። ነገር ግን በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ በዓመት አንዴ መስከረምን ጠብቀው እንደ ሚመጡ እንጂ ዓመቱን ሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚኖሩ ግንዛቤ የለም። ምክንያቱም የመስቀል ወፍ በደረቅ ወቅት ቀላማቸው ፈዛዛ ሆኖ ከሴት ወፎች ጋር በአካልም ሆነ በቀለም ብዙም ሳይለዩ ተመሳስለው በመኖራቸውና በቀላሉ በአካባቢው መኖራቸውን ማስተዋል ባለመቻሉ ነው።

ለምን ወፎች ቀለማቸውን ይቀይራሉ?

ወፎች ቀለማቸውን የሚቀይሩት በመራቢያ ወቅታቸው እንደሆነ አብዛኛዎቹ ምሁራን ይስማሙበታል። የመስቀል ወፎች በሚራቡብት ወቅት ላባቸውን ቀስብቀስ በሙሉ በማርገፍና በሌላ ቀለም ላባ በመቀየር ወይም የጅራት ላባቸውን በማሳደግ አምረውና በአካል ግዙፍ መስለው በመታየት ተቃራኒ ፆታን ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት ነው። ይህ ሂደትም በዓመት አንዴ በመስከረም ወር ብቅ ብለው ከዚያ በኋላ የሚጠፉ አዲስ የወፍ ዝርያዎች ያስመስላቸዋል።

ለምን የመስቀል ወፍ ተባሉ?

የመስቀል ወፍ የሚለው ስያሜ ወፎቹ ለየት ብለው የሚከሰቱበት ወቅት ኢትዮጵያ በዓመት አንዴ ከምታከብረው የመስቀል በአል (ደመራ) ጋር የሚገጣጠም በመሆኑ የተሰጣቸው ስያሜ እንደሆነ ይታመናል።

የመስቀል ወፍ አንድ ናት?

የመስቀል ወፍ አንድ ብቻ ሳትሆን በርከት ያሉ የወፍ ዝርያዎችን የሚያጠቃልል የወል ስም ነው። እነኝህ በቪዱይዴ (Viduidae) እና ፕሎሴይዴ (Ploceidae) በተባሉ ሁለት ቤተሰቦች (Families) ውስጥ የሚመደቡ ዝርያዎች ናቸው። በብዛት ከሚታወቁት የመስቀል ወፍ ዝርያዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

1. የሰሜናዊው ቀይ ቢሾፕ (northern red bishop)
ይህ ወፍ ቢሾፕ (Bishop) ተብለው ከሚጠሩት የወፍ ዝርያዎች የሚመደቡ ሲሆን በሳይንሳዊ ስሙ ኢዩፕለክተስ ፍራንሲስካነስ (Euplectes franciscanus) ተብሎ ይጠራል።

2. ስፒል-ጅራት ኋይዳህ ወፍ (Pin-tailed whydah bird)
ይህ ወፍ ኋይዳህ ተብለው ከሚጠሩት የወፍ ዝርያዎች ሲመድብ ሳይንሳዊ ስሙ ቪዱዋ ማክሮራ (Vidua macroura) ይባላል። በመራቢያ ወቅት ወንዱ ስፒል-ጅራት ኋይዳህ ወፍ የጅረቱ ላባ ከሰውነቱ ሁለት እጥፍ በማሳደግ ለየት ብሎና ገዝፎ በመታየት እንስቷን ለመሳብ ይሞክራል።

3. ባለርዥም ጅራት ፓራዳይዝ ኋይዳህ ወፍ (Long-tailed paradise whydah)
ይህ የመቀል ወፍ በሳይንሳዊ ስሙ ቪዱዋ ፓራዲሴያ (Vidua paradisaea) ተብሎ ይጠራል። ወንዱ ጥቁር የሁነ ረዥም የጅራት ላባ ያበቅልና ለየት ያለ ቀለም ሲኖረው ከመራቢያ ወቅት ውጭ ግን ከሴቷ ተመሳሳይ አካልና ቀልም ይኖርዋል።

4. የመንደር ኢንዲጎ ወፍ (Village indigobird)
ይህ ወፍ በአብዛኛው በሀገራችን የሰሜኑ ክፍል በብዛት የሚገኝ ሲሆን በሳይንሳዊ ስሙም ቪዱዋ ቻልይቢታ (Vidua chalybeeta) ተብሎ ይጠራል።

(By Mengistu Wale: Research Associate (MSc), Zoological science)
Ethiopian Biodiversity Institute (EBI), Animal Biodiversity Directorate)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *