የሳይንስ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ የሰው እና ባዮስፌር ሪዘርቮች የምክክር መድረክ ተካሄደ


የሳይንስ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ የሰው እና ባዮስፌር ሪዘርቮች የምክክር መድረክ ተካሄደ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በሰው እና ባዮስፌር ሪዘርቮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡፡

በመድረኩ ላይ የአካባቢ ደንና አየር ንበረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕ/ር ፍቃዱ በየነ፣ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማርዮ (ዶ/ር)፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የብዝሀ ሕይወት ማዕከላት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ተገኝተዋል፡፡

የመድረኩ ዓላማ የኢትዮጵያ ባዮስፌር ሪዘርቮች ያሉበት ይዞታ፣ ተግዳሮቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና አስተዳደራዊ ተሞክሮዎች ዙሪያ ለመምከር እንዲሁም የብሔራዊ የሰውና የባዮስፌር ሪዘርቭ ኮሚቴ ስራን አጠናክሮ ለማስቀጠል ነው፡፡

ሰውና ባዮስፌር የተሰኘው ፕሮግራም እ.አ.አ በ1971 በዩኔስኮ የተመሰረተ ሲሆን በሰዎችና በተፈጥሮ ሀብት መገኛ በሆነው አካባቢያቸው ያለውን ትስስር ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የተሻለ ማድረግን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) የሰውና የባዮስፌር ፕሮግራም በመንግስት ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር የተዋወቀው እ.አ.አ በሚያዝያ ወር 1987 ዓ.ም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማሪዮ (ዶ/ር) እንደተናገሩት በኢንስቲትዩቱ የደንና ግጦሽ መሬት ዕፅዋት ብዝሀ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ስር የባዮሰፈር ሪዘርቭ ኬዝ ቲም የተዋቀረ ሲሆን በመቱና በባህርዳር የብሀ ሕይወት ማዕከላትም ውስጥ ተቋቁሞ  ከኮሚሽን መስሪያ ቤቱ ጋር በመመካከር ሥራውን በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

የአካባቢ ደንና አየር ንበረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕ/ር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዝሀ ሕይወትና በተፈጥሮ ሀብት የታደለች በሆኗን አስታውሰው ከእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን መካከል ደግሞ ባዮስፌር ሪዘርቮቻችን በዋናነኝት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕ/ር ፍቃዱ አክለውም ባዮስፌር ሪዘርቮች የጀነቲክ ሀብትንና ሥርዓተ-ምህዳርን ማንበር፤ ሳይንሳዊ ምርምር ማካሄድና የክትትል ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም በዙሪያው ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ ቀዳሚ ዓላማዎቹ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ ይህ ሰውና ባዮስፌር ሪዘርቭ ፕሮግራም ከፍተኛ የሳይንስ ባህል ግንባታን የያዘ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ረጅም አመታትን ያስቆጠረ በመሆኑና የሳይንስ ሳምንት መበሆኑም ጭምር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

በሀገራችን እ.አ.አ. ከ2010 ጀምሮ አምስት ባዮስፌር ሪዘርቮች ማለትም ያዩ የቡና ጫካ፣ የሸካ ደን፣ ከፋ፣ ጣና ሀይቅ እና ማጃንግ ደን በ UNESCO አለም አቀፍ የትብብር ካውንስል ተመዝግበው የማንበር፣ የልማት፣ የምርምር፣ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

በምክክር መድረኩ ላይም ማጃንግ፣ ከፋ እና ያዩ ባዮስፌር ሪዘርቮች የሚገኙበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ እያከናወኗቸው ያሉ ስራዎች እንዲሁም ተግዳሮቶቻቸው ለመድረኩ ተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡

በቀረቡት ጽሁፎችና አጠቃላይ በኢትዮጵያ ባዮስፌር ሪዘርፎች ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *