ብዝሀ ሕይወትን ሊጠብቅ የሚችልው ጠንካራና ተቆርቋሪ የሰው ሀይል ምንጭ ነው ተባለ፡፡

የህዝብ ክንፍና ባለድርሻ የምክክር መድረክ
አቶ ማስረሻ የማነ

ብዝሀ ሕይወትን ሊጠብቅ የሚችልው ጠንካራና ተቆርቋሪ የሰው ሀይል ምንጭ ነው ተባለ፡፡

የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የህዝብ ክንፍና ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄደ፡፡

በርካታ ባለድርሻ አካላትንና  የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ሰራተኞችን ባሳተፈው የምክክር መድረክ ላይ በመገኘት የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማርዮ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በብዝሀ ሕይወት ሀብት ክምችት ከሚታወቁት 20 የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነችና ከአፍሪካ በዚሁ ሀብት ከሚታወቁት አምስት ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት እንደምትጠቀስ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የሀገሪቷን ብዝሀ ሕይወት ሀብቶችን መጠበቅ፣ በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ የጀነቲክ ሀብት አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነትን ለማስፈን ዓላማ አድርጎ የሚሰራ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባሏት የተፈጥሮ ሀብት ፀጋ ብርቅዬ የብዝሀ ሕይወት መገኛ ሀገር ብትሆንም ይህ የተፈጥሮ ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የመመናመን ችግሮች እየደረሰበት እንደሚገኝ በመድረኩ ከተነሱ ሀሳቦች አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ካለፉት 44 ዓመታት ጀምሮ የተለያዩ የእፅዋት ጀነቲክ ሀብቶችን በመሰብሰብ፣ በመጠቀም ለተጠቃሚ በማድረስ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑንም ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የህዝብ ክንፍና የባለድርሻ አካላትን የምክክር መድረክ ያዘጋጀበት ዋና ምክንያት ኢንስቲትዩቱ እየሰራ ያለውን ስራ ግንዛቤ በመፍጠር ለወደፊቱ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው  እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር መለሰ ተናግረዋል፡፡

አቶ ማስረሻ የማነ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የኢንስቲትዩቱን የስድስት ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለታሳታፊዎች ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ 5 ዋና እና 9 ደጋፊ የስራ ሂደቶች፣ 7 ማዕከላት፣ 3 እፅዋት አፅዶች፣ 1 ተለዋጭ ጅን ባንክ፣ 30  ማህበራዊ ዘር ባንኮች እንዳሉት በመግለጽ በስድስት ወራት የተሰሩ የስራ ክንውኖችን አቅርበዋል፡፡

ከህዝብ ክንፍ አካላት ጋር የሚከናወኑ ተግባር አመልካች እቅድ ማዘጋጀት፣ የውስጥ ተገልጋይ እርካታ ዳሰሳ ፣ የማዕከላት እቅድ ከዋናው መስሪያ ቤት እቅድ ጋር የማስተሳሰር ስራ መሰራቱ የኢንስቲትዩቱ ጠንካራ ጎኖች እንደሆኑ አቶ ማስረሻ ተናግረዋል፡፡

 

ኢንስቲትዩቱ በርካታ ስራዎችን በሚሰራበት ወቅት ካጋጠሙት ተግዳሮቶች እንደ ለምርምር የሚያስፈልጉ የኬሚካል ግዢ ሂደት አለመጠናቀቅ፣ የበጀት ችግር፣ ወርሀዊ የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም መገምገሚያ መድረክ ዝቅተኛ መሆን እንደውስንነት ተጠቅሷል፡፡

በመድረኩም የዋና ስራ ሂደቶች ተግባር፣ ሀላፊነትና የየዘርፉ የተመረጡ የምርምር ስራዎች ለባለድረሻ አካላት የቀረቡ ሲሆን በቀረቡት ፅሁፎች መነሻነት ኢንስቲትዩቱ ስለሚያከናውናቸው ስራዎች፣ ስለአየር ንብረት ለውጥ፣ ለተሳታፊዎች አዲስ ስለሆኑ ቃላቶች፣ ስለ ኢንስቲትዩቱ ተልዕኮና ዓላማ እንዲሁም በርካታ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተው የኢንስቲትዩቱ የሚመለከታቸው ስራ ሀላፊዎች ምላሽ አግኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *